የዴንቨር ሊቀ ጳጳስ ‘ጥላቻን ብቻ የሚያቀጣጥሉ’ ጥቃቶች እንዲቆሙ ጠየቁ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በዩናይትድ ስቴትስ፣ ኮሎራዶ ግዛት ውስጥ በምትገኘው ቦልደር ከተማ ግንቦት 24 ቀን 2017 ዓ.ም. በጋዛ የእስራኤል ታጋቾችን ለመደገፍ እና ለማስታወስ ሰልፍ በወጡ ሰላማዊ ሰዎች ላይ በደረሰው ጥቃት በጣም ማዘናቸውን የገለጹት የዴንቨር ሊቀ ጳጳስ ሳሙኤል አኳይላ፥ 'ጥቃቱ በተለየ ሁኔታ አይሁዳውያን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ላይ ኢላማ ያደረገ ይመስላል' ብለዋል።
በኮሎራዶ ግዛት እሁድ ዕለት ጋዛ ውስጥ በሃማስ ታግተው የሚገኙ እስራኤላውያንን ለማሰብ “ለህይወታቸው እንሩጥ” በሚል ስያሜ በተደረገው የእግር ጉዞ ላይ የ45 ዓመቱ ግብፃዊ “ነፃ ፍልስጤም” እያለ ተቀጣጣይ ፈንጂ" (Molotov cocktails) ህዝቡ ላይ በመወርወር ጥቃት ማድረሱን እና በጥቃቱ 12 ሰዎች ቆስለው፥ ስድስቱ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል መግባታቸው ተገልጿል።
ተጠርጣሪው ጥቃቱን ለመፈጸም ከአንድ ዓመት በላይ ማቀዱን፣ በተለይም “ጽዮናዊ ቡድን” ሲል የገለጸውን የህብረተሰብ ክፍል ኢላማ ማድረጉን የገለጸ ሲሆን፥ ግለሰቡ ቃለ መጠይቅ በተደረገለት ወቅት ‘ሁሉም እንዲሞቱ እንደሚፈልግ እና ምንም እንደማይጸጸት፥ ከዚህ የባሰ ጥቃት መፈጸም እንደሚፈልግ’ ለኮሎራዶ አቃቤ ህግ ተናግሯል።
የኤፍ.ቢ.አይ. ኃላፊዎች ድርጊቱን "የሽብር ጥቃት" ሲሉ ገልጸው፥ ወኪሎቻቸው በቦታው ምርመራ እያደረጉ መሆናቸውን እና በተጠርጣሪው ላይ ክስ መመስረቱን አስታውቀዋል።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩሉ ድርጊቱን በአይሁዶች ላይ ያነጣጠረ አስፈሪ ፀረ-ሴማዊ የሽብር ጥቃት ነው ሲል ድርጊቱን አውግዟል።
“ይህ ዓይነቱ ጥቃት መቆም አለበት”
ሊቀ ጳጳስ አኳይላ ጉዳዩን አስመልክተው ሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ፣ “ይህ ዓይነቱ ጥቃት ጥላቻን የሚያቀጣጥል በመሆኑ መቆም እንዳለበት” ገልጸው፥ በዚህ ዘግናኝ ጥቃት ለተጎዱ ሰዎች በሙሉ ጸሎት እንዲደረግ በመጋበዝ፥ “እንዲህ ያለውን ጥላቻ በመቃወም ጌታ መጽናናትን፣ ፈውስንና ሰላምን እንዲያመጣ እንለምናለን፣ እርስ በርሳችን እንድንዋደድ የሚጠራንን የእግዚአብሔርን ድምፅ እንስማ!” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ሊቀ ጳጳስ አኳይላ የሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ አስተምህሮትን በመጥቀስ በሰጡት መግለጫ፥ ቤተክርስቲያን ከአይሁዶች ጋር የምትጋራውን የአንድ አባት ልጅነትን እያሰበች እና በፖለቲካዊ ምክንያቶች ሳይሆን በወንጌል መንፈሳዊ ፍቅር በመመራት በማንም ሰው ላይ የሚደርሰውን ስደት ሁሉ እንደማትቀበል ጠቅሰው፥ በማንኛውም ጊዜ እና በማንኛውም ሰው አይሁዶች ላይ ያነጣጠረ ጥላቻን፣ ስደትን እና ፀረ ሴማዊነትን እንደሚቃወሙ ገልጸዋል።
‘ኖስትራ አታቴ’ ተብሎ የሚጠራው ይህ የሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ሰነድ ስለ ቤተ ክርስቲያን እና ክርስቲያናዊ ያልሆኑ ሃይማኖቶች ሲገልጽ “ቤተ ክርስቲያን በሰዎች ላይ የሚደርሰውን ማንኛውንም ዓይነት መድልዎ ወይም በዘራቸው፣ በቀለማቸው፣ በኑሮአቸው ወይም በሃይማኖታቸው ምክንያት የሚደርስባቸውን ትንኮሳ ትምህርተ-ክርቶሳዊ ባለመሆናቸው አጥብቃ ትቃወማለች” በማለት ይገልፃል።