ፈልግ

ብጹዕ ፒየር ጆርጆ ፍራሳቲ እና ብጹዕ ካርሎ አኩቲስ፤ ብጹዕ ፒየር ጆርጆ ፍራሳቲ እና ብጹዕ ካርሎ አኩቲስ፤ 

ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የስምንት ብጹዓን እና ሰማዕታት ቅድስናን አጸደቀች

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ከቅድስት መንበር የቅድስና ጉዳዮች ጳጳሳዊ ምክር ቤት የቀረበላቸውን የቅድስና መዝገብ ተመልክቶ ማረጋገጫን የሚሰጥ የካርዲናሎች መማክርት መደበኛ ጉባኤን ጠርተዋል። ጉባኤው የቀረበለትን መዝገብ ከተመለከተው በኋላ የስምንት ብፁዓን እና ሰማዕታት ቅድስናን በማረጋገጥ ለመላዋ ቤተ ክርስቲያን በይፋ የሚታወጅበትን ቀን ወስኗል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ለመጀመሪያ ጊዜ ማለትም ዓርብ ሰኔ 6/2017 ዓ. ም. ከጠሩት የካርዲናሎች መማክርት ጋር ሆነው ለስምንት ብፁዓን የቅድስና ፈቃድ ሰጥተው፥ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፥ የብጹዕ ፒየር ጆርጆ ፍራሳቲ እና የብጹዕ ካርሎ አኩቲስ ቅድስና አንድ ላይ እሑድ ጳጉሜ 2/2017 ዓ. ም. እንደሚታወጅ አስታውቀዋል።

ሁለቱ ወጣቶች፥ የመጀመሪያው የሃያኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ እና ሁለተኛው የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ቅዱስ ሲሆን፥ የሁለቱ ወጣቶች ቅድስና በምዕመናን መካከል በነበራቸው ታላቅ ፍቅር ምክንያት ሲጠበቅ የቆየ እንደሆነ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ለመጀመሪያ ጊዜ የቅድስና ማዕረግን አጸደቁ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ለመጀመሪያ ጊዜ የቅድስና ማዕረግን አጸደቁ   (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከዚህ በፊት አሳውቀዋል

ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ኅዳር 11/2017 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ባቀረቡበት ዕለት፥ የወጣት ፒየር ጆርጆ ፍራሳቲ እና የወጣት ካርሎ አኩቲስ ቅድስናን ለታዳሚዎቻቸው ማሳወቃቸው ይታወሳል።

ብጽዕናው በአሲሲ ከተማ ቅዳሜ መስከረም 30/2013 ዓ. ም. የታወጀለት ካርሎ አኩቲስ፥ በዓሉ በፋሲካ ሁለተኛ እሁድ ማለትም ሚያዝያ 19/2017 ዓ. ም. እንዲሆን ቀጠሮ የተያዘለት ቢሆንም ዕለቱ የታዳጊ ወጣቶች ኢዮቤልዩ የሚከበርበት በመሆኑ ወደ ሌላ ጊዜ መዛወሩ ይታወሳል። የወጣት ፒየር ጆርጆ ፍራሳቲ የቅድስና አዋጅ የወጣቶች ኢዮቤልዩ በዓል ፍጻሜ ማለትም ሐምሌ 27/2017 ዓ. ም. እንዲሆን ተደርጓል። የእነዚህ የሁለቱ ወጣቶች ቅድስና ይፋ የሚሆነው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ዓርብ ሰኔ 6/2017 ዓ. ም. በወሰኗቸው ቀናት እንደሚፈጸም ተረጋግጧል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በቅዱሳን መዝገብ ውስጥ እንዲገቡ የወሰኗቸው እነዚህ ሁለት ወጣቶች ከተለያዩ ዘመናት የተውጣጡ፣ ፍጹም የተለያየ ሕይወት ይመሩ የነበሩ፣ ነገር ግን ለኢየሱስ ክርስቶስ ባላቸው ፍቅር እና ሕይወታቸውን ለተነኩ ሰዎች ያንን ፍቅር ለማካፈል ባላቸው ችሎታ አንድ እንደሆኑ ተነግሯል።

ሊቀ ጳጳስ ብሩክ ኢኛሲዮ ሹክራላህ ማሎያን
ሊቀ ጳጳስ ብሩክ ኢኛሲዮ ሹክራላህ ማሎያን

ቅድስናቸው በጥቅምት ወር የሚታወጅላቸው ሰባት ብሩካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ዓርብ ሰኔ 6/2017 ዓ. ም. በጠሩት የካርዲናሎች መማክርት ጉባኤ ላይ ቅድስናቸው የሚታወጅላቸው ሌሎች ሰባት ብሩካን ይፋ በማድረግ ዕለቱንም መወሰናቸው ታውቋል።በኦቶማን ግዛት በአርሜኒያ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1915 ዓ. ም. በሰማዕትነት የተገደሉ የአርሜኒያ ካቶሊካዊ ሊቀ ጳጳስ ኢኛሲዮ ሹክራላህ ማሎያንን ጨምሮ የሰባት ብፁዓን የቅድስና ቀንን ወስነዋል። ከእነዚህ መካከል ሌላኛው፥ ጃፓኖች የክርስትና እምነት እንዳይሰብክ ቢያግዱትም ነገር ግን የትምህርተ ክርስቶስ መምህርነቱን በመቀጠሉ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1945 ዓ. ም. በሰማዕትነት የሞተው ምእመን ፒተር ቶ ሮት ነው። በዚህም ብፁዕ ፒተር ቶ ሮት የፓፑዋ ኒው ጊኒ የመጀመሪያው ቅዱስ እንደሚሆን ታውቋል።

ብፁዕ ፒተር ቶ ሮት
ብፁዕ ፒተር ቶ ሮት

ቅድስናቸው ከሚታወጅላቸው ሰባቱ መካከል ሦስቱ ገዳማውያት ሲሆን፥ ቪንቼንሳ ማርያ ፖሎኒ፥ በጣሊያን ቬሮና የምሕረት እህቶች ተቋም መሥራች፣ ማርያ ዴል ሞንቴ ካርሜሎ ሬንዲልስ በቬነዙዌላ የኢየሱስ አገልጋዮች ማኅበር መሥራች እና እህት ማርያ ትሮንካቲ፥ የእመቤታችን ማርያም የክርስቲያኖች ረዳት የሴቶች ገዳም አባል እንደነበረች ታውቋል።

በመጨረሻም ሌሎች ሁለት ምዕመናን በቅዱሳን መዝገብ ውስጥ ከገቡት መካከል ሲሆኑ፥ ባርቶሎ ሎንጎ፥ በጣሊያን ፖምፔ የሚገኝ የዝነኛው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ መሥራች እና ሆሴ ግሬጎሪዮ ሄርናንዴዝ ሲስኔሮስ፣ ቬኔዙዌላዊ ዶክተር እና የቅዱስ ፍራንችስኮስ ሦስተኛ ማኅበር አባል ሲሆን፣ የተቸገሩትን በማከም አልፎ ተርፎም የመድሃኒት ወጪዎችን ከኪሱ የሚከፍል በመሆኑ “የድሆች ሐኪም” በመባል የሚጠራ እንደ ነበር ታውቋል።

ቪንቼንሳ ማርያ ፖሎኒ፥
ቪንቼንሳ ማርያ ፖሎኒ፥
13 Jun 2025, 16:49