ፈልግ

በፈረንሳይ-ኢል ዴ ፍራንስ ክልል ሚገኙ የስምንት ሀገረ ስብከቶች ካህናት የኢዮቤልዩ በዓላቸውን ሲያከብሮ በፈረንሳይ-ኢል ዴ ፍራንስ ክልል ሚገኙ የስምንት ሀገረ ስብከቶች ካህናት የኢዮቤልዩ በዓላቸውን ሲያከብሮ  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የፈረንሳይ ካኅናት ለጋስነትን እና ፍቅርን እንዲላበሱ አበረታቱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ክልል ለሚያገለግሉ ካህናት በላኩት መልዕክት፥ አስቸጋሪ የሆነ የቤተ ክርስቲያን እና ማኅበራዊ ሁኔታዎች ውስጥ ወንድማማችነትን እና አንድነትን እንዲያሳድጉ በማለት የፈረንሳይ ካኅናትን አበረታትተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የካኅናት ኢዮቤልዩ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለፓሪስ ከተማ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት እና ቀሳውስት ሐሙስ ግንቦት 28/2017 ዓ. ም. የተላከው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ መልዕክት በኖትርዳም ካቴድራል ውስጥ በቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተነቧል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመልዕክታቸው ውስጥ፥ የኢዮቤልዩ በዓላቸውን የሚያከብሩ፥ በፈረንሳይ-ኢል ዴ ፍራንስ ክልል ሚገኙ ስምንት ሀገረ ስብከቶች የሚያገለግሉ ካህናት ያስተነተኑበትን “የካኅናት ማኅበር” ድንጋጌ 60ኛ ዓመትን አስታውሰዋል።

በቅርቡ የፈረንሳይ ሐዋርያዊ ተልዕኮ አገልግሎት ጳጳስ አድርገው የሾሟቸው የክሬቴይል ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዶሚኒክ ብላንዤ ባነበቡት መልዕክት ውስጥ ቅዱስነታቸው እንደገለጹት፥ “ለተሰጣችሁ የእግዚአብሔር ሕዝብ የምታበረክቱት ሐዋርያዊ አገልግሎት ቀጣይነት እንዲኖረው አባታዊ ፍቅር እና ልባዊ ማበረታቻዬን እገልጻለሁ” ብለዋል።

በዚህ ዘመን ካኅናትን የሚያጋጥሟቸው ፈታኝ የቤተ ክርስቲያን እና ማኅበራዊ ሁኔታዎችን ጠንቅቀው እንደሚያውቁም ተናግረዋል።

ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተደጋጋሚ ይናገሩት የነበረውን ምክር በማስታወስ፥ ካኅናት ሕይወታቸውን እና አገልግሎታቸውን ለኢየሱስ ክርስቶስ ይበልጥ ጠንካራ፣ ግላዊ እና እውነተኛ በሆነ መሠረት ላይ እንዲያቆሙ፣ እንዲሁም ለማኅበረሰባቸው ለጋስ እና ነጻ ፍቅርን በማሳየት ዘወትር ቅርብ፣ ርኅሩኅ፣ ገር እና ትሁት እንዲሆኑ አደራ ብለዋል።

“ገና ቅዱሳን ባትሆኑም ነገር ግን ይህን በመድረጋችሁ የኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝ አገልጋዮች ትሆናላችሁ” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ከቤተ ክርስቲያን ርቀው የሚገኙትን ሰዎች ልብ መንካት፣ እምነትንም ማትረፍ እና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንዲገናኙ መርዳት ትችላላችሁ” ብለዋል።

በመቀጠልም፥ ካኅናቱ በመካከላቸው ክኅነታዊ ወንድማማችነትን እንዲያሳድጉ፣ ከጳጳሶቻቸው ጋር ያለውን የበጎነት ትስስር እንድትጠብቁ እና ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ያለማቋረጥ እንዲጸልዩ አደራ ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ካኅናቱ የክኅነት ምስጢርን በተቀበሉባት ዕለት ራሳቸውን ለእግዚአብሔር በስጦታነት ማቅረባቸውን እንዲያስታውሱ የመንፈስ ቅዱስን እገዛ በጸሎት ጠይቀዋል።

በመጨረሻም፥ ለካህናቱ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጥበቃን እና የቀደሙት የፓሪስ ከተማ ቅዱሳን ካህናት እና ጳጳሳት ሁሉ አማላጅነት በመለመን መልዕክታቸውን አጠቃልለዋል።

በፈረንሳይ - ኢል ዴ ፍራንስ ክልል በሚገኙ ስምንት ሀገረ ስብከቶች ውስጥ የሚያገለግሉ ካኅናት፥  የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1965 ዓ. ም. ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ ድንጋጌ ውስጥ የካኅናት አገልግሎት እና ሕይወት በማስመልከት በጻፉት ላይ እንዲያሰላስሉ ተጋብዘዋል።

ከዚያም ሐሙስ ግንቦት 28/2017 ዓ. ም. ወደ ኖትር-ዳም ካቴድራል የኢዮቤልዩ ንግደት በማድረግ ከሰዓት በኋላ በኅብረት ሆነው መስዋዕተ ቅዳሴን አሳርገዋል።

 

06 Jun 2025, 15:10