ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ለብጹዕ ፍሎሪበርት እናት ሰላምታ ሲያቀርቡ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ለብጹዕ ፍሎሪበርት እናት ሰላምታ ሲያቀርቡ፣  (@Vatican Media)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ለአፍሪካ ሰላም የብጹዕ ፍሎሪበርት አማላጅነት ጠየቁ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ መላዋ ቤተ ክርስቲያን የወጣት ፍሎሪበርት ቧና ቹይ ብጽዕናን ይፋ ባደረገች ማግሥት፥ ወጣቱ በእግዚአብሔር ላይ በነበረው እምነት እና በሰላም ገንቢ ምሳሌነቱ ላይ በማስታወስ ባደረጉት ንግግር፥ ብጹዕ ፍሎሪበርት በኪቩ፣ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት እና በመላው አፍሪካ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ ለነበረው ሰላም እንደሚጸልይ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በመላዋ ቤተ ክርስቲያን ብጽዕናው የታወጀለት የፍሎሪበርት ቧና ቹን የጸሎት ሕይወት በማስታወስ ሰኞ ሰኔ 9/2017 ዓ. ም. ባሰሙት ንግግር፥  “ይህ አፍሪካዊ ሰማዕት ወጣቶች በብዛት በሚገኙባት አፍሪካ ውስጥ የሰላም እርሾዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ያሳያል” ብለው፥ “ይህ የኮንጎ ወጣት የምእመናን እና የወጣቶች ምስክርነት ውድ ዋጋን አጉልቶ ያሳያል ሲሉ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ይህን የተናገሩት፥ እሁድ ሰኔ 8/2017 ዓ. ም. አመሻሽ በሮም በሚገኝ በቅዱስ ጳውሎስ ባዚሊካ ውስጥ በቀረበው የፍሎሪበርት ብጽዕና መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ለተገኙት መንፈሳዊ ነጋዲያን  እንደ ሆነ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በንግግራቸው፥ “አንድ ወጣት ማንኛውንም ጥቃት መፈፀም የሚችል አስተሳሰብ በሰፈነበት ውስጥ ሙስናን ለመቃወም የሚያስችል ጥንካሬን ከየት አገኘ?” ሲሉ ጠይቀው፥ እጆቹን ከማንኛውም ክፉ ተግባር ንጹሕ ለማድረግ በጸሎት፣ የእግዚአብሔርን ቃል በማዳመጥ እና ከወንድሞቹ እና እህቶቹ ጋር በመገናኘት ባገኘው ሕሊና ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

የቅዱስ ኤጂዲዮ መንፈሳዊነት

ብጹዕ ፍሎሪበርት የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበረሰብ መንፈሳዊነትን ይከተል እንደ ነበር ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ሟቹ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የወጣቱ በጎ ተግባራት በሦስት ቃላት እነርሱም፥ ጸሎት፣ ድሆች፣ ሰላም የሚሉ እንደ ነበር አስታውሰዋል።

ድሆች በሙሉ የብጹዕ ፍሎሪበርት ሕይወት ዋና ማዕከል መሆናቸውን ገልጸው፥ ብጹዕ ፍሎሪበርት በአገሪቱ በሚካሄደው ጦርነት ምክንያት ወደ ጎማ ለተሰደዱት የጎዳና ተዳዳሪ ሕጻናትን ለመርዳት ራሱን እንደሰጠ እና ከእነዚህም መካከል ብዙዎቹ የተናቁ እና ወላጅ አልባ እንደ ነበሩ አስታውሰዋል።

“ብጹዕ ፍሎሪበርት እነዚህን ሕጻናት “በኢየሱስ ክርስቶስ ቸርነት ይወዳቸው ነበር” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “ስለ ሕጻናቱ ሰብዓዊ እና ክርስቲያናዊ ዕድገት ያስብ እና ይጨነቅ ነበር” ብለው፥ የብጹዕ ፍሎሪበርት ጥንካሬ ለጸሎት እና ለድሆች ባለው ታማኝነት ማደጉን እና የሰላም ሰው እንደ ነበረም አስታውሰዋል።

"ኢየሱስን ከልብ አዳምጧል"

“ብጹዕ ፍሎሪበርት በመከራ እና በዓመፅ በተሰቃየ እንደ ኪቩ ባለ አካባቢ ለሰላም ታግሏል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ በየዋህነት ድሆችን በማገልገል፣ ወዳጅነትን በመለማመድ እና በተከፋፈለ ማኅበረሰብ ውስጥ መገናኘቱንም አጉልተዋል።

“ይህ ወጣት ለክፋት ጨርሶ እጅ አልሰጠም” በማለት አጥብቀው የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “በቅዱስ ወንጌል ቃል ለማደግ እና ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ህልም ነበረው” ብለው፥ ብዙ ወጣቶች እንደተረሱ እና ምንም ተስፋ እንደሌላቸው ቢሰማቸውም ነገር ግን ፍሎሪበርት፥ “ኢየሱስ ክርስቶስ በቃሉ፥ ‘ወላጅ እንደሌላቸው አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ’ ያለውን አድምጧል” ብለዋል።

“ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው ሰላም ለኪቩ፣ ለኮንጎ እና ለመላው አፍሪካ ሕዝብ”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው ሰላም ለኪቩ፣ ለኮንጎ እና ለመላው አፍሪካ ሕዝብ” የሚለውን በማሰብ እንደተናገሩት፥ ብጹዕ ፍሎሪበርት በታላቅ እምነት እና በእግዚአብሔር ላይ ባለው ተስፋ፥ “በእግዚአብሔር የተዘነጋ መሬት የለም!” ማለቱን አስታውሰው፥  በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና በብፁዕ ፍሎሪበርት አማላጅነት፥ “ሲጠበቅ የነበረው ሰላም ለኪቩ፣ ለኮንጎ እና ለመላው አፍሪካ ሕዝብ በቅርብ ይመጣል!” ብለዋል።

16 Jun 2025, 17:39